እየመሸ ነው ። የጨፈገገው ምሽት! ፀሃይ ወደማደሪያዋ ካሽቆለቆለች ረፈደ። ደመና በግራጫ ሰማይ ላይ ረብቦ፤ክበቡ ለአይን እየከበደ ሲሄድ ደስ የማይል ስሜት በልብ ላይ ይጭራል። ዝናብ ለረጅም ገዜ ሲዝንብ ቆይቶ ያቆመ ቢሆንም በጨለማው ሽንቁር ውስጥ ሰማዩ እንዳኮረፈ ያስታውቃል። ያለሁበት ክፍል ጨልሞ የሚታየው ከኮምፒተሪ መስኮት የሚወጣውን የፈዘዘ ብርሃን ወድጄዋለሁ። ከኮምፒተሪ ጀርባ ባለው ሰፊ መስኮት ዓለም እንደዝርግ ሳህን ፈሶ ከፊቴ ተሰትሯል። ሁሌም ባተሌ የሆነው የ 395 አውራ ጎዳና ከውሏቸው በሚመለሱ ተሽከርካሪዎች ቀይ የኋላ መብራት መፈናፈኛ አጥቶ ታፍኗል። አይኖቼ የብርሃናቸውን ነጠብጣብ እየተከተለ ይሮጣል። ሃሳቤም እንዲሁ።…………………
ሃሳብ መቼም ቀንድ እንጂ ጭራ የለውም። ይህን ልክ የአንድን መኪና የኋላ መብራት አይን እስከሚችለው ድረስ ተከትሎ ከሌሎች መሰሎቹ ጋር ተደበላልቆ ገጹ ሲጠፋ ያንን በመሸነፍ ስሜት አቁሞ ሌላ ደግሞ በቅርብ ያለን የተሽከርካሪን የኋላ መብራት እንደመከተል አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ቁም ነገሩ በመጀመሪያውና በኋልኛው መሃከል ያሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የኋላ ተሽከርካሪ መብራቶችን ልብ ሳንላቸው ማለፋቸው ነው። ከነዛ ልብ ሳንላቸው፣ሳናያቸው እና ሳንመለከታቸው ካለፉት የተሽከርካሪ መብራቶች መሃከል አንድ የተለየ መብራት ያለው ተሽከርካሪ አምልጦን ይሆናል። ምን ይሆን!?...........ማን ያውቃል!.........ለሕይወት እንዲሁም ለዓለም ያለንን አመለካከት የሚለውጥ ሃሳብ ሳያጭር ይቀራል!።
እዚህ ላይ ሁለት ሺ ዓመት ወደኋላ ተጉዘን በጥቁር እና ነጭ ቀለማት ጥንታዊቷ አክሱም ውስጥ በኋልኛው ግዜ ቅዱስ የሚሆነውን የሊቁን ቅዱስ ያሬድ ታሪክ መመልከት እንችላለን። እንግዴህ ያኔ ትምህርት አልገባ ብሎት በተደጋጋሚ ፈተና የወደቀው ወጣት ተስፋ በመቁረጥ ከአካባቢው መጥፋት ፈልጓል። ቀኑን ሁሉ በጠራራ ፀሃይ ሲጓዝ ውሎ ስለደከመው በአንድ ትልቅ የዛፍ ጥላ ስር አርፏል። የአካባቢው ፀጥታ፣ በዛፎቹ ዙሪያ ያለው ነፋሻማ አየር ለፍጹም የግል ተመስጦ የሰጠ ነው እንበል። መቼም ነፍሱ ለትልቅ ነገር የተፈጠረ ነው እና በአረማሞ ከፊት ለፊቱ ባለው ዛፍ ላይ የሚርመሰመሱት የጉንዳን መንጋዎች ላይ አይኑን ተክሎ ከፈጣሪው እና ከራሱ ጋር በጥሞና ሙግት ገጥሟል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩት የጉንዳን ሰራዊት ከመሪት ወደዛፉ ቅጠል እና ቅርንጫፍ በሰልፍ የሚያደርጉትን ጉዞ ፤የተበጣጠሰ ሃሳቡን እላያቸው ላይ አሳፍሮ፤ የሚሄደውን በመሸኘት እንደገና አዲስ ከሚመጣው ጋር ሽቅብ ወደላይ ይነጉዳል። በዚህ ፍጹማዊ እርጋታን በተላበሰ ተመስጦ የሚሞግተው ሃሳብ ግልጽ ያለና የጠራ በመሆኑ ነፍሱ ሰማያተ-ሰማያት በመውጣት የዕውቀትን ሚስጥር እና ከዛም የሚገኘውን ማስተዋል ለመጠየቅ አስችሎታል። ከሁሉም አስገራሚው ነገር ከፈጣሪ ምላሽ ያገኘበት ሁኔታ እና ያንን ለመተርጎም የተቸረው ተሰጥኦ ነበር።
ወጣቱ ቅዱስ ያሬድ ከእነዛ የዛፉን ግንድ ሽቅብ ወደላይ ከሚወጡት ጉንዳኖች መሃከል በተደጋጋሚ ለመውጣት እየሞከረ ከመሃል ሳይደርስ የሚከሰከስ ጉንዳን አይኖቹን ስቦታል። እየጀመረ ሳይጨረስ ከመሃል እየተንደረደረ ቁልቁል የሚወድቀው ጉንዳን ሳያሰልስ ለመውጣት የሚያደርገውን ሙከራ ገርሞት በንቃት መቁጠር ይዟል። አንድ………॥ሁለት……॥ሦሥት…………।ሰባተኛውን መቁጠር እንደያዘ፤ ጉንዳኑ ሙከራው ተሳክቶላት ጉዞውን ከሌሎች ጉንዳኖች ጋር በመቀላቀል በአሸናፊነት ቀጠለ። ይህኔ የዕውነትም የዕውቀትም መገለጥ ወደሱ ይመጣል። “ ይህ ቅንጣት ፍጡር ተፍጨርጭሮ አሰበበት ለመድረስ የቻለ እኔ በእግዜር ዓምሳል የተፈጠርኩ የፈጣሪ ታላቅ ስራ፡ እንዴት ትምህርቴን መጨረስ ያቅተኛል!? ”
ከዚህ በኋላ ያለው ታሪኩ እንደሚታወቀው ትምህርቱን ትቶ ለመጥፋት ያሰበውን በመቀየር ወደ ትምህርት ቤቱ በመመለስ ያቋረጠውን ትምህርት ጨርሶ ከነ ሞዛርት እና ቤትሆቨን የሚበልጥ የዜማ ሊቅ ይወጣዋል:: ተመስጦ ከማስተዋል ጋር ሲዋሃድ ይሏል እንዴህ ነው!!
ተመስጦ ወደ ውስጣችን አለያም ወደ ነፍሳችን ጥልቀት በመመልከት ይጀምራል። በእርግጥ እንደሚባለው ወደ ውስጣችን መመልከት ያስፈራል። የነፍሳችን በር ጨለማ የዋጠው፡ በነውጥ የተሞላ ውካታ ነው። ያንን አልፈው እጥልቅት ያሚገኘውን ሰላም መመልከት የሚችሉ ድፍረቱ የታደላቸው በጣም ጥቄቶች ብቻ ናቸው።
ሰው ወደ ነፍሱ ጥልቀት ዘልቆ ማየት ከቻለ ውጫዊውን ቁሳዊ ዓለም መገንዘቡ እርግጥ ነው። ወደ ውስጥ ለመመልከት ሳይደፍሩ ውጫዊውን ዓለም መረዳቱ የማይታሰብ ነው። የነፍስህን ሙግት ለማቅረብ ወደ ውስጥህ ጥልቀት በተመስጦ ታያለህ። ምላሹ ግን ያለው ቁሳዊው ዓለም ላይ ነው። የነፍስህ ጥልቀት ከውጫዊው ዓለም የምታገኘውን ምላሽ ለመረዳት የሚያስችልህን ማስታዋል ይለግስሃል።
ወደ ውስጥህ በተመስጦ በተመለከትክ ቁጥር ምንጩ ወዴት እንደሆነ ወደ ማታውቀው ብርሃን እየቀረብክ ነው። በህይወትህ ለመጀመሪያ ግዜ እራስህን መገንዘብ ትጀምራለህ። አንተ ማንም አይደለህም፡ እራሱን የምታየው ብርሃን እንጄ! ደግሞም የዕሳቤህና የግንዛቤህ የንጋት ብርሃን ነጸብራቅ ነህ!!!
ሆኖም ሁሉም ነገር ግን ያልፋል። ዕሳቤህም᎐᎐᎐᎐᎐᎐᎐የተገነዘብከውም ቁሳዊ ዓለም!! የሚቀረው ብርሃኑ ብቻ ነው። በሊቁ ቅዱስ ያሬድም የሆነው ይሄው ነበር።
የከርሞ ሰው ይበለን!!
0 comments:
Post a Comment