በመጋቢት ወር 1953 የቀድሞዋ ሶቬዬት አንባገነን መሪ ጆሴፍ ስታሊን ጭንቅላቱ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ምክንያት ለህልፈተ ህይወት ሲዳረግ የሩሲያ ጋዜጦች ለታላቁ መሪያቸው የሚቆጥቡት እንባ አልነበራቸውም። ልባቸው በሃዘን የተነካ ንግግር አድራጊዎች ስታሊንን ‘ ጄኔየስ እና የሩሲያን ህዝቦች የታደገ አምላክ’ ሲሉ ገለጹት። በኋላም አስከሪኑ በቀዩ አደባባይ ከሌኒን አጠገብ በክብር ሲያርፍ ሺዎች በዕንባ ሊሰናበቱት ሰልፍ ያዙ።
በ1956 ዓ/ም ኔኪታ ክሩቼቭ መጋረጃውን ገፎ “ ስታሊን ለ43 ሚሊዮን ሰዎች መገደል፣ መጥፋት እንዲሁም በባርነት መጋዝ ምክንያት የሆነ ጭራቅ ” መሆኑን እስኪገልጽ ድረስ ማንም ምንም ለማለት አልደፈረም። በርግጥ ክሩቼቭ በፓርቲው ስብሰባ ላይ ደፍሮ እስታሊንን የሚወነጅል ንግግር ሲያደርግ የደበቀው እና ጨምሮ ያልተናገረው ሌላ ታሪክ እንዳለ ግልጽ ነበር። ‘ ዛሪ……ዛሪ የሚወጡ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ’ ይለናል የ World’s Great Mysteries ደራሲ John Pinkney ‘ ታላቁ አንባገነን ህይወታቸውን ለማዳን እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር የሚጀመረውን የኒኩሊየር ጦርነት ለማስቀረት ሲሉ አራት ፍርሃት የዋጣቸው ጓደኛሞች በአይጥ መርዝ መርዘው ሳይገድሉት አልቀሩም። ’
ታሪኩ እንደዚህ ነው……………………………………………………
የህይወት ዘመን የሶቬት ህብረት መሪ በተዝናና ስሜት ላይ ነው ያለው። በክሪሚሊን ቤት መንግስት ባለው የግል ሲኒማ ማሳያ የኮሜዲ ፊልም እያየ በታላቅ ደስታ ውስጥ የነበረ ሲሆን አሁን ደግም ምቾት ባለው ክፍል ውስጥ ከፓርቲው የማዕከላዊ አባላት 4 ሰዎች ጋር እየተዝናና ነው። እንሱም ላቨረንቲይ በሪያ፣ ጂኦርጂ ማለንኮቭ፣ ኒኪታ ክሩቼቭ እንዲሁም ኒኮላይ ቡልጋኒን ናቸው።
እንደ ሁሌው ስታሊን ጨዋታውን ተቆጣጥሮታል። ዙሪያውን የከበቡት የፖለቲካ ጓዶቹ ብዙውን ግዜ በንግግሩ ፈገግ በማለት ወይ በአድናቆት ጭንቅላታቸውን በመነቅነቅ አልያም የሚጠጡትን መጠጥ ከመጎንጨት ባለፈ ድምጻቸው አይሰማም። በጠረጲዛው ላይ ብራንዲ፣ ቮድካ እንዲሁም ሊላ የአልኮል መጠጥ አይታይም። መሪው በማዘዙ ምክንያት ዛሪ የማጃሪ ወይን ተራ ሲሆን ከጥሩ ጨዋታ ጋር የተሻለ እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ክብ ስርተው ከተቀመጡበት ወንበር ጀርባ ባሉ ሁለት ረጃጅም ጠረጴዛዎች አጠገብ አንዳች ነገር ቢፈጠር ቅጽበታዊ እርምጃ ለመውሰድ በተጠንቀቅ የቆሙ የክብር ዘቦች አሉ። ከእንሱ አንዱ አሌክሲ ራይቢን በኋለኛው ግዜ ስለዛች ቀን ምሽት An Iron Soldier የተባለ ማስታዋሻ የጻፈ ሲሆን ስለተከሰተው ነገር ብዙ የተብራራ ነገሮችን ይዟል።
በዚያች ምሽት አለ- አንዳች የውስጥ እውቀት ከውጭ ቆሞ ለሚያይ ታዛቢ የስታሊንን ወዳጆች ደስተኛነት እና ፍጹም በደህንነት ውስጥ መኖራቸውን ቢገምት አይፈረድበትም። እውነታው ግን ሁሉም በፍራቻ ባህር ውስጥ ስምጠው ነበር። እያንዳንዳቸው ይህ ጨካኝ እና ምህረት የለሽ ሰው በማንኛውም ግዜ ተነስቶ ሊገላቸው አለያም ከከባድ ስራ ጋር ማጎሪያ ቦታዎች ሊያግዛቸው የሚችል አደገኛ ፍጡር መሆኑን አላጡትም። አራቱ ጓደኛሞች እስታሊን በፓርቴው ማዕከላዊ አባላት ላይ የማጽዳት ዘመቻ ሊያካሂድ እንዳሰበ መረጃው ደርሷቸዋል። ስለጉዳዩ በመጀመሪያ አንስቶ ከጓደኞቹ ጋር ለመወያየት የደፈረው ክሩቼቭ ነበር። ሁሉም ስታሊን አደገኝነቱ በዙሪያው ላሉ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ለሩሲያ እንዲሁም ከዛ ባለፈ ለዓለምም ጭምር መሆኑን ተረድተዋል። ቀደም ብሎ በግላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የኑክሌር ግጭት ለመጀመር መፈለጉን ግልጽ አድርጎላቸዋል። ሩሲያ ደሃና ደካማ አገር በመሆኗ ጦርነቱን የማሸነፍ ተስፋ እንደሌላት ያውቃሉ። ደሞም በእርግጥ ማንም አሸናፊ አይኖርም። ይህን ወደ አርማጌዴኦን የሚያመራ የዕብደት እርምጃ እስታሊን እንዲጀምር ማንም አይፈቅድለትም። ስለዚህ ስታሊን መሞት አለበት። ወሳኙ ምላጭ ዛሪ ምሽት መሳብ አለበት።
ሪይቢን በዚሁ ማስታወሻው እንደገለጸው የተከበሩ እንግዶቹ አስክ ንጋቱ አስር ሰዓት ቆይተው ሲወጡ እስታሊን ወደ አልጋው አመራ። ኢቫን ክሩስታሌቭ የሚባል በቅርቡ የተሾመ የክብር ዘብ እንባገነኑን አጅቦ ወደክፍሉ ከወሰደው በኋላ ክፍሉን ከውስጥ በላያቸው ላይ ዘጋው። በኋላ ላይ የክብር ዘቡ ለባልደረቦቹ “ በእንደዚህ ሁኔታ የመጀመሪያዬ ቢሆንም…………… ደህና……… ጓድ እስታሊን ምሽቱን ስለማይፈልጉን ሁላችንም ወደመኝታ እንድንሄድ ነግረውኛል ” አለ።
ለነዚህ የደህንነት ሰዎች ዜናው አስገራሚ ነበር። ይህ በጠላቶቹ ጥላ ፍርሃት አድሮበት በማንኛውም ሰዓት እርምጃ የሚወስድ ሰው ሁሌም በ ሃያ አራት ሰዓት የድህንነት ጥላ ውስጥ ነበር የሚኖረው።ጠባቂዎቹ እሱን እንዲጠብቁ ብቻ አይደለም ትዕዛዝ የተሰጣቸው፤ እርስ በእርሳቸውም እንዲሳለሉ ጭምር!!
በጠዋቱ አራት ሰዓት ስለቀኑ ዕቅዳቸው ለመወያየት በወጥ ቤቱ ተሰባሰቡ። በሚያስደንቅ ሁኔታ ግን ይህ ክሩስታሌቭ የተባለ አዲስ ሰው ወደ ቤቱ ሂዷል። የወጥ ቤቱ ቼፍ ጌታው እንደመጣ ቁርሱን ለማሰናዳት በተጠንቀቅ ላይ ነው። ነገር ግን እስከ ጠዋቱ አምስት ሰዓት የስታሊን መምጣት አልታየም። ወዲያው እኩለ ቀን አለፈ…….ሰባት……..ስምት…….ዘጠኝ ሰዓት ። የክብር ጠባቂዎቹ አሁን መጨነቅ ጀመሩ። ነገር ግን ማንም እስታሊንን ከእንቅልፉ በመቀስቀስ ሊረብሸው አልፈለገም። በማያስፈልግ ሁኔታ ከእንቅልፉ መቀስቀስ ቅጣቱ የከፋ ሊሆን ይችላል።
ከምሽቱ አስራ ሁለት ተኩል ላይ ከደህንነት አባላት አንዱ የስታሊን ማረፊያ ክፍል መብራት ማየቱን ተናገረ።አዛዡ ፓቬል ሎጋቼቭ “ ተመስገን አምላኬ!...........ሁሉም ነገር ደህና ነው ” አለ። ለብዙ ሰዓታት መብራቱ መብራቱን ቀጥሏል። እስታሊን ግን ከክፍል አልወጣም። በስጋት የሚናጡት ዘቦች አንዳች እርምጃ ሊወስዱ አልቻሉም። ወዲያው ከምሽቱ አራት ሰዓት ሲሆን መልዕክተኛ ከማዕከላዊ ኮሚቴ መልእክት ይዞ መጣ። ማንኛቸውም መልዕክቱን ይዞ ለመግባት የደፈረ የለም። መልእክተኛው መልእክቱን አሁኑኑ ባይሰጡት ሊደርስባቸው የሚችለውን ቅጣት እንዳይረሱት አስታወሳቸው። ፓቬል ሎጋቼቭ ንግግሩን አቋርጦ ይዞ ገባ።
ከአርባ አራት ዓመታት በኋላ ለስፑትኔክ የሰኔ ወር 1997 ዕትም እንዲህ ሲል ገልጾታል።
“………….እንዲህ አልኳቸው ፤ ‘ ደህና……መልካም ተመኙልኝ…..ልጆች! ’ ብዬ ወደስታሊን ክፍል አመራሁ። ሁሌም ወደሱ ክፍል ስንገባ ድምጽ እያሰማን ነው የምንገባው። በጸጥታ ድምጽ ሳታሰማ ስትገባ እይወድም። በራስህ ተማምነህ እና እርግጠኛ ሆነህ ብዙም አትኩረት ሳትስብ መራመድ አለብህ። ያለዚያ ጥሩውን ወታደር ሽዌክን ማስመሰል እንድታቆም ይነግርሃል።………………… በሩን እስከኮሪደሩ በስፋት ከፈትኩ እና ወደ ትንሿ ክፍል ስመለከት እስታሊን ወለሉ ላይ ተዘርሯል። ቀኝ እጁ ታጥፏል። እንዳየሁት በቅዝቃዜ ደረቅሁ። ልረዳው አሰብኩ። እጆቼ እና እግሮቼ ግን ሊታዘዙኝ አልቻሉም። “ ጓድ እስታሊን …..ምንድ ነው የተፈጠረው? ” ስል ጠየቅሁ። ወዲያው ሰውነቱ በሽንቱ መርጠቡን አየሁ። “ ዶክተር ልጥራ? ” አልኩት። በማጉረምረም “ ዶክ…..ዶክ ” አለ። አዕምሮው ማሰብ አቁሞ ፤የሚናገረውን ጥፍቶበት ነበር።
ሎጋቼቭ መሬት ላይ የወደቀ የፕራቭዳ ጋዜጣ ዕትም እና አስራ ሁለት ሰዓት ላይ መቁጠሩን ያቆመ የኪስ ሰዓት ወለሉ ላይ መውደቁን ልብ ብሏል። ጠረጴዛው ላይ ያልተከፈተ የማዓድን ውሃ በጠርሙስ ይታያል። እስታሊን ሩሁን ስቶ ከመውደቁ በፊት ከአልጋው በመነሳት መብራቱን አብርቶ ውሃውን ለማግኘት መራመዱን ገምቷል።
ሩሲያዊው የታሪክ ጸሓፊ ኤድቫርድ ራድዚንስኪ “ ስታሊን ” በሚለው መጸሃፉ የአይን እማኞችን ቆጥሮ በወቅቱ ስለተፈጠረው ድንጋጤ የተሻለ አብራርቶታል…….
…………በፍርሃት የተወዥናበረው ሎጋቼቭ እራሱን እንደምንም ለማረጋጋት እየሞከረ በግዜው ለሁለት ቀን እረፍት ላይ ለነበረው ለበላይ አለቃው የዳቻ አዛዥ ሻሮስቴን ስልክ ደወለ። አስደንጋጩ ነገር የተነገረው ሻሮስቴን በፍጥነት ወደ ዳቻ በመመለስ ወለሉ ላይ ተጋድሞ የሚያንኮራፋውን አንባገነን በአትኩረት ሲመለከተው ቆየና ምቾት እንዲሰማው በማለት ወታደሮቹ አንስተው ሶፋው ላይ እንዲያስተኙት አዘዛቸው። ቀጥሎም ወደ ኬጂቢ ጽህፈት ቤት ደውለ። ስልኩን ያነሳው የኬጂቢ የበላይ ሃላፊ በድንጋጤ ማንኛውንም ሃላፊነት እንደማይወስድ በመቃወም ተናገረ። እንዲያውም ሻሮስቴን እራሱ ባለፈው ማታ አብረውት ላመሹት እንግዶቹ ማሊንኮቭ እና በሪያ እንዲደውልላቸው ትዕዛዝ አስተላለፈለት። “ እነሱ ምን እንደሚሰሩ ያውቃሉ። ” አለው።
ሻሮስቴን ለበሪያ ደውሎ የደረሰውን ድንገተኛ ሁኔታ ሲገልጽለት እንዲህ አለው። “ ለማንም እንዳትናገር! ጓድ ስታሊን ታመዋል። ”
ሰዓታት ነጎዱ። እየሞተ ያለውን መሪ መጥቶ የሚያየው ባለስልጣን ጠፋ። በላዩ የለቀቀው ሽንቱ ከሶፋው እየተንጠባጠበ የወለሉን ምንጣፍ አራሰው። ይህ ሁሉ ሲሆን የደነገጡ የክብር ጠባቂዎቹ ዙሪያውን ከበው ይመለከቱታል።
ኔኪታ ኩሩቾቭ በጻፈው ማስተዋሻው ደግሞ ከዚህ የተለየ ይነግረናል………..
………… ማሊንኮቭ በድንገት ደወለልኝ። “ ተመልከት! የደህንነት ሰዎች ከስታሊን ቤተ መንግስት ተጨንቀው ይደውላሉ። እስታሊን አንድ ነገር ሳይሆን አይቀርም!፧ ወደዛ ሂድ። እኔም መጣሁ። ለቡልጋኒን እና ለበሪያ ስለደወልኩላቸው እነሱም በአጭር ግዜ ይደርሳሉ። ” አለኝ።
መኪናዬ እንዲዘጋጅልኝ አዘዝኩና ወዲያውኑ ወደ ቤተ መንግስቱ አመራሁ። እግሪ ገና መሪት ከመርገጡ “ ምንድን ነው የተፈጠረው!? ” ስል ዘቦቹን ጠየቅሁ። “ በዚህ ሰዓት ( ከምሽቱ አምስት ሰዓት ) እስታሊን ስልክ ደውሎልን ሻይ ያዝ ነበር። ዛሪ ግን የለም። ” ሲሉ አብራሩልኝ። ”
ክሩቼቭ እንደገለጸው ከባልደረባው ጋር በቀጥታ ወደ ዳቻ ( የስታሊን መኖሪያ ) ሄደ።
“ የዳቻው ዘቦች ጥሩ ያልሆነ ነገር እንደተፈጠረ እና እስታሊንም መኝታው ላይ እንዳለ ነገሩን። እናም በዛ ሁኔታ መመልከቱ ስህተት መስሎ ስለተሰማን ሁላችንም ወደቤታችን ተመለስን። ”
ለአስራ ሶስት ሰዓታት የታላቋ ሶቬት ህብረት የበላይ መሪ ጆሴፍ ስታሊን የህክምና እርዳታ ሳያገኝ እዳሪው ላይ እንደተጋደመ ቀረ። በመጨረሻም ተስፋ የቆረጡ ጠባቂዎቹ ስለደወሉለት ክሩቼቭ አስር ሃኪሞች ወደ ዳቺያ ሄደው እንዲያክሙት ትዕዛዝ ሰጠ። ነገር ግን ራይቢን አስጠርቶ ሲያሳያቸው ሁሉም ወሳኙን ህክምና ለማድረግ ፈሩ። በሚያንኮራፋው አንባገነን ዙሪያ የደም ግፊቱን ለመለካት ወይ ሌላ ምርመራ ለማድረግ ጨንቋቸው እርስ በእርስ ይጠባበቁ ጀመር። እንዲያውም የሚንቀጠቀጠው የጥርስ ሃኪም የበሽተኛውን የፎቶ ፍሪም ሳያስበው መሪት ላይ ጣለው።
አንዱ ሃኪም “ ቪኖግራዶቭ እዚህ መገኘት የለበትም እንዴ!? ” ሲል ጠየቀ። ቪኖግራዶቭ የስታሊን የግል ሓኪም ነበር።ምክትል አዛዡ ሎጋቼቭ ጠጋ ብሎ በሹክሹክታ ፤
“ ያማ አስቸጋሪ ነው። ባለፈው ሳምንት ተይዟል። ” አለው። ይህ ግዜ ብዙዎቹ የህክምና ባለሞያዎች በመንግስት ላይ ታሴራላችሁ በሚል ክስ ወደ ዘብጤያ የሚወርዱበት ወቅት ነበር። እሱም ያ ዕጣ ደርሶታል;
ስታሊንን ሊያክሙት የመጡት ሓኪሞች ሳንባ የሚያሰራ የብረት ማሽን አብሯቸው ነበር። ነገር ግን ፍጹም አልተጠቀሙበትም። የስታሊን ልጅ ስቬትላና እንደገለጸችው “ ያ ትልቅ ነገር ሃኪሞቹ አይናቸውን ከፍተው አፍጥጠው እያዩት ምንም ሳይሰራ አጠገባቸው እንደተቀመጠ ቀረ። ”
በ1972 ዓ/ም የአካዳሚ አባል የነበረው ፕሮፊሰር ማያሲንኮቭ ያንን ግዜ ወደ ኋላ ተመልሶ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል።
“………..ማሌንኮቭ እየተፋጠነ ወደ ውስጥ ገባ። ፊቱን አልቦታል። የበሽተኛውን ህይወት ለማስረዘም ማንኛውንም ነገር እንድናደርግ ነገረን። በዛን ሰዓት ሁላችንም የህዝቡን ጭንቅላት ለማዘጋዠት እና አዲስ መንግስት ለመመሥረት ግዜ እንደሚያስፈልግ ገብቶን ነበር። ስታሊን ያንኮራፋል። ባልጋው ላይ እንደተጋደመ ውሉ የጠፋ ሃሳብ ፊቱ ላይ እየበነነ ሲሄድ ይታያል። የማዕከላዊ ኮሚቴ የፕሪዚዲየሙ አባል የሆነው ቮሮሺሎቭ “ ጓድ ስታሊን ሁላችንም ጓደኞችዎ እና ወዳጆችዎ አጠገብዎ ነን። የተከበሩ ጓደኛዬ እንዴት ይሰማዎታል? ”አለው። ነገር ግን የስታሊን አይኖች ስሜታቸውን መግለጽ እያቆሙ ነበር። ቀኑን ሙሉ መርፊ ስንወጋው እና ጋዜጣዊ መግለጫ ስንጸፍ አሳለፍን። የፖሊት ቢሮ አባላት ወደ ሚሞተው ሰው ክፍል ገቡ። የበታች ባለስልጣናት በበሩ አጮልገው ይመለከታሉ። በደንብ አስታውሳለሁ፤ ከነሱ አንዱ ክሩቼቭ ነበር።………..”
ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ላይ ከአዶልፍ ሂትለር ያልተናነሰው የጅምላ ጨፍጫፊ አረመኔ እስከወዲያኛው አሸለበ። በመላው ሩሲያና ከዛም ባሻገር ሚሊዮኖች ሊያነቡለት ተዘጋጁ። የምዕራቢያዊያን የምርምር ተቋማት ስታሊን ለሰው ልጅ ላደረገው መልካም ነገር ታላቅነቱን የሚገልጽ አጫጭር ጹሁፎች ፣ መጸሃፍት እና ንግግሮችን በማሰማት አጮሁለት። በሳይቤሪያ እና በሉቢያንካ መታጎሪያ ቦታዎች በግፍ ለሚሰቃዩ ምስኪን እስረኞች ግን የቅዠት ዘመናቸው የሚያበቃበት ግዜ እንደደረስ ተስፋ አደረጉ።
እንግዺህ ከዚህ ሁሉ በኋላ ማንኛውም አንባቢ የሚያነሳው ጥያቄ ይኖራል። ምንድ ነው በዕርግጥ እስታሊን ላይ የደረሰው? ኦፊሻሊ እንደተነገረው ጭንቅላቱ ውስጥ የደም መፍሰስ ስላጋጠመው ነው የሞተው? ወይስ በሰው ተገደለ?
ያኔ ዕውነቱ ባይታወቅም እስታሊን ተመርዞ ለመሞቱ የሚገልጹ የሩሲያና የምዕራቢያዊያን የታሪክ ተመራማሪዎች እየተበራከቱ ነው።ሁሉም እንደሚሉት ጓደኞቹን በግዜ ወደመኝታቸው እንዲሄዱ የነገራቸው አዲሱ የክብር ዘብ ክሩስታሌቭ የአንባገነኑን ነፍስ ለመሸኘት ተንቀሳቅሷል። ከአለቃው የኬጂቢ ሃላፊ ላቭሪንትይ በሪያ በደረሰው ትዕዛዝ መሠረት የተኛውን አንባገነን በሰው ልጅ ላይ የጭንቅላት ደም መፍሰስ የሚያስከትለውን የአይጥ መርዝ ሳይወገው እንዳልቀረ ተገመቷል።
Stalin’s Last crime በሚለው መጻሃፋቸው ፕሮፊሰር ብረንት ሲገልጹ፤ ማሌንኮቭ፣ በሪያ፣ ክሩቼቭ እና ቡልጋኒን አንባገነኑን ለማስወገድ የተደረገውን ሴራ ለማሳካት ባለ ኃይላቸው ተንቀሳቅሰዋል። ስታሊን እራሱ ዕቅዱን በገለጸው መሰረት ሁለተኛውን ሽብር በመጀመር በመቶ የሚቆጠሩ የፓርቲ ባልደረቦቹን እና ሌሎች በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሩሲያውያንን ለመጨፍጨፍ ተዘጋጅቷል። ከዚህ ሁሉ የከፋው አደገኛ ነገር ግን መላውን ዓለም ለማጥፋት ማቀዱ ነበር። አራቱ ሴረኞች ከራሳቸው ህይወት የበለጠ ያስፈራቸው የኑክሌር እልቄት እርምጃውን እንዲወስዱ አድርጓቸዋል ይላሉ ብራንት።
የ Stalin መጸሃፍ ደራሲ ኤድቫርድ ራድዚንስኪ ከ ፓቬል ሌጋቼቭ ጋር ያደረጉትን ንግግር እንዲህ ሲል ዘግቦታል።….
“…………….እስታሊን ከመሞቱ ከሳምንት በፊት ‘ አሜሪካ ትወረናለች ብልህ ታስባለህ? ’ ሲል ጠየቀኝ። እንደማይደፍሩ መለስኩለት። ያ - አበሳጨው። በኋላ ላይ ወደ እኔ መጥቶ እንዲህ አለኝ። ‘ አዎ!....ይወሩናል!! ’
እንደዛ ሲለኝ በግልጽ ከፊቱ ላይ እንደዛ እንዲሆን መፈለጉን ማንበብ ችዬ ነበር። ”
የሆኖ - ሆኖ ይህ የWorld’s Great Mysteries ደራሲ ስለ ስታሊን አሟሟት የሚተርከውን ምዕራፍ የሚዘጋው አንባገነኑ በተፈጥሮ ሞት ይሙት ወይ በባልደረቦቹ ሴራ ተጠልፎ በመመረዝ፤ ሞቱ ግን በዓለም ታሪክ ታይቶ የማያቅ ሊመጣ የነበረውን የሰው ልጅ ዕልቄት ማስቀረት ችሏል።